Wednesday, 23 November 2016

እውነት ቁርአን አልተበረዘም?

ብዙ የሙስሊም ሙህራንና ሰባኪዎች መጽሀፍ ቅዱስ የተበረዘና ትክክለኛ ፈጣሪ ቃል እንዳልሆነና በተቃራኒው ቁርዓን ምንም ያልተበረዘ ነጥብ እንኳን ያልተቀየረ መሆኑን በኩራት ሲናገሩ በመሆኑም ትክክለኛው ፈጣሪ ቃል መሆኑን ሲገልጹ ይሰማል፡፡ እውነታው ግን ይሄ ነው ወይ? እውነት አሁን ያለው የቁርአን ጽሁፍ በመሀመድ ጊዜ የነበረው ነው ወይ?
1. የቁርአን ታሪክ
የመጀመሪያው የቁርዓን መገለጥ የመጣው በ610 ዓ.ም እንደሆነ ይታመናል፡፡ መሀመድ ከዛን አመታት (23 አመታት) ጀምሮ ለተከታዮቹ ከላይ የወረዱለትን የቁርዓን መገለጦች እያስታወሰ እንደቆየ ብዙ የሙስሊም ጸሀፊዎች አሰፍረውታል፡፡ እንዳይጠፉ በማሰብም የተወሰኑትን የቁርዓን ጽሁፎች በሞቱ እንሰሳት አጥንት፣ በጠፍጣፋ ድንጋዮች፣ በዘንባባ ቅጠል ይጻፉ ነበር፡፡
መሀመድ ከሞተ በኋላ አቡበከር ወደ ያማማ ጦርነት ስለዘመተና በዛ ጦርነት ሁሉንም የቁርአን በቃል የሚያስታውሱ ሰዎች የሞቱ ስለሆነ እንዲሁም የመሀመድ ከሊፋዎች አቡበከር፣ ኡመር እና ኡስማን በጦርነቱ ላይ ትኩረት ስላደረጉ ያስታወሳቸው አንዳለነበር ኢብን አቢ ዳውድ በኪታብ አል ማሳሂፍ መጽሀፋቸው ገልጸውታል፡፡
ሳሂህ አል ቡኻሪ በሀዲስ ቁጥር 4986 አቡበከር ከያማማ ጦርነት በኋላ የተቀሩት የቁርዓን ጽሁፎች ከመጥፋት አንዲድኑ በማሰብ ለዛይድ ቢን ታህቢት አንዲሰበስብ ይህንን ሚና በመስጠት፡ ዛይድም እነዚህን ጽሁፎች በ634 ዓም አካባቢ ሰብስቦ እንደጨረሰ ዘግቦታል፡፡
አቡበከር ከሞተ በኃላ የተሰበሰቡትን ጽሁፎች ለሳህፋ (የመሀመድ ሚስት) ሰጥቷት አንደሞተ በዚሁ ሀዲስ ተዘግቧል፡፡
በሳሂህ አል ቡኻሪ ሀዲስ ቁጥር 4987
ኡመር ሞቶ ኡስማን ስልጣን ከያዘ በኋላ ያ ማለት መሀመድ ከሞተ 19 አመታት በኋላ ማለት ነው፤ በቁርአን ቂርኣት ዙሪያ ትልቅ ክርክር መነሳት ጀመረ፡፡ ይህንን የተረዳው ኡስማን ሃፍሳ ከአቡበከር የተቀበለችውን የቁርአን ጽሁፍ አንዲሁም ሌሎች ሰዎች ጋ ያሉትን ጽሁፎች አቀናብረው እንዲጽፉ ለዛይድ ቢን ታህቢት፣ ለአብዱላህ ቢን አዝ ዙቤይር፣ ለሳይድ ቢን አል አስ እና ለአብዱሮህማን ቢን ሃሪዝ ተልእኮ ሰጥቷቸው አሰባስበው ጽፈው ጨረሱ፡፡ ከዛም ይህንን ተሰባስቦ የተጻፈ የቁርአን እትም በማባዛት ኡስማን ለሁሉም የሙስሊም ግዛቶች እንዲሰራጭ ካደረገ በኃላ የተበጣጠሱ እና ያልተሟሉ የቁርአን ጽሁፎችን እንዲቃጠሉ ተደረገ፡፡ (ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት ያለው የቁርአን ጽሁፍ የኡስማን ስብስብ ነው ማለት ነው፡፡)
በመሀመድ ሱሃባዎች መካከል ክርክር
አዲስ ኡስማን ባሰባሰበው የቁርአን ጽሁፍ ዙሪያ በመሀመድ ጓደኞች መካከል ትልቅ ክርክር ተነስቶ ነበር፡፡
አል ቡኻሪ በሀዲስ ቁጥር 3808 መሀመድ አንድ ጊዜ ቁርአን መማር ከፈለጋችሁ መማር ያለባችሁ ከአራት ሰዎች ነው፡፡ እነሱም ከአብደላህ ቢን ማሱድ፣ የአቡ ሁዘይፋ ባሪያ ከነበረው ሳሊም፣ ሙዘህ ቢን ጀበል እና ኡቤይ ቢን ካዕብ ነው፡፡ ሲል ዘግቦታል፡፡ የሚገርመው በዚህ የቁርአን ስብስብ ቅራኔ የነበረው መሀመድ ትልቅ አድናቆት የሰጠው አብደላ ቢን ማሱድ ነበር፡፡ ኢብን መሱድ የቁርዓን ምዕራፎች 111 መሆን እንዳለባቸው ተናግሯል፡፡ ኡስማን ያሰባሰባቸው ጽሁፎች ግን 114 ምዕራፎች ናቸው፡፡ አንደ መሱድ እምነት ሱረቱል ፋቲሃ፣ ሱረቱል ፈለቅ እና ሱረቱል ናስ ቁርአን ውስጥ መካተት የሌለባቸው ምዕራፎች እንደሆኑ በዚሁ ሃዲስ ተዘግቧል፡፡
ኢብን ሳድ በኪታብ አልታብቃት አልከቢር ሁለተኛ መጽሃፋቸው አንደጻፉት ኢብን መሱድ የኡስማን ስብስብ ጽሁፎች መሀመድ ካስተማረው ጋር ሲተያይ የብዙ መቶ ቃላት ልዩነት ያለውና የተጭበረበረ እንደሆነ መናገሩን ጽፈዋል፡፡ ይህን ቁርአን የሚቀሩ ሰዎች ትልቅ ወንጀል እየሰሩ ናቸው፡፡ ቁርአን መሀመድ አንዳስተማረው ቢቀሩት ነበር ደስ የሚለው ሲል መናገሩን ኢብን ሳድ በዚሁ መጽሃፋቸው ጨምረው ጽፈውታል፡፡ ታዲያ ለዚህ ማታለል ምን መልስ መስጠት ይቻላል ሙስሊም ወንድሞች፡፡
ምክንያቱም ኡስማን እንዲሰበሰቡ ያደረጋቸው የቁርዓን ጽሁፎች መሀመድ በሚኮራባቸው ጓደኞቹ እንኳን የተጣጣሉና የተጨበረበሩ እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡
ሌላው አዲሱ የኡስማን ቁርአን ቅራኔ የነበረው መሀመድ የሚኮራበት ግለሰብ ኡቤይ ኢብን ካዕብ ነበር፡፡ ኡቤይ የኡስማን ቁርአን ሁለት ምዕራፎች ይጎሉታል ሲል መናገሩን ቡኻሪ ዘግቦታል፡፡
ቡኻሪ በሀዲስ ቁጥር 5005 የመሀመድ ሁለተኛ ከሊፋ የነበረው ኡመር ኡቤይ ቁርአን እውቀቱ የተሻለ እንደሆነ ብናውቅም እሱ ሲቀራቸው የነበሩትን ጽሁፎች አንዳንዶቹን ትተናቸዋል ሲል ተናግሯል፡፡ኡቤይ ግን እኔ እነዚህን ቂርአቶች የሰማኋቸው ከአላህ መልዕክተኛ ስለሆነ መተው እንደሌለባቸው መናገሩን ዘግቧል፡፡
ታዲያ እንዴት ሆኖ ነው ቁርአን አልተበረዘም ማለት የሚቻለው?
የጠፉ ምዕራፎች
አንድ ጊዜ ኢብን ኡመር የሁለተኛው ከሊፋ ኡመር ልጅ ሰዎች ሁሉንም ቁርአን አውቀናል፡፡ እያሉ ሲያወሩ ይሰማል፡፡ ኢብን ኡመርም ይህንን ሲሉ ለነበሩ ሰዎች ማንም ሰው ቁርአንን ሙሉ በሙሉ አውቃለሁ ማለት የለበትም ምክንያቱም ብዙዎቹ የቁርአን ጽሁፎች የጠፉ ስለሆነ በማለት ማስጠንቀቁን አቡ ኡቤይድ ፌዴይል አል ቁርአን በተሰኘ መጽሐፋቸው ጽፈውታል፡፡
ሳሂህ ሙስሊም በሀዲስ ቁጥር 2286 በበኩሉ ከመሀመድ ጓደኞች አንዱ አቡ ሙሳ በስንፍና ምክንያት ሁለት የቁርአን ምዕራፎች መጥፋታቸውን መናገሩን ዘግቦታል፡፡
የጠፉ አንቀጾች
ቁርአን ከጠፉ ምዕራፎች በተጨማሪ ካሉት ምዕራፎች ውስጥ የጠፉ አንቀጾች እንዳሉ ነው የሙስሊም ታሪክ ጸሀፊዎች ያሰፈሩት፡፡ ለምሳሌ የመሀመድ ተወዳጅ ሚስት አይሻ የሱረቱል አህዛብ 2/3ኛ የሚሆኑ አንቀጾች መጥፋታቸውን ተናገራለች፡፡ አቡ ኡቤይድ፡ ኪታብ ፌይዴል አል ቁርአን መጽሐፋቸው ሱረቱል አህዛብ መሀመድ በነበረበት ወቅት 200 አያዎች (verses) የነበሩት ሲሆን ቀደም ብለን እንደገለጽነው በያማማ ጦርነት ውስጥ አብዛኞቹ ቁርአንን በቃል የሚያስታወሱ ሰዎች ስለሞቱ ማስተካከል ስላልተቻለ አሁን ያሉት 73 አያዎች (verses) ብቻ ናቸው፡፡ ሲሉ ገልጸውታል፡፡

የጠፉ አያዎች (verses)
አይሻ አሁንም ስለጠፉ (verses) ትነግረናለች፡፡ በሱናን ኢብን ማጃህ ሀዲስ ቁጥር 1944 ‘በድንጋይ መውገር‘ እና አዋቂ ሰውን 10 ጊዜ ጡት ማጥባትን አስመልክቶ የወረዱ አያዎች (verses) አይሻ ትራስ ስር ደብቃው እንደነበረ በበግ መብላቱን መናገሯን ተዘግቧል፡፡ ስለዚህ እንዚህ አያዎች (verses) በአሁኑ ቁርአን ውስጥ የሉም፡፡ ምክንያቱም በአይሻ በግ ስለተበሉ፡፡
የጠፉ ዓረፍተ-ነገሮች
ቁርአን ዓረፍተ-ነገሮቹ ያልተሟሉ ሱራዎች ያሉበት መጽሀፍም ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁለት ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡
በሱረቱል አህዛብ ቁጥር 6 “ነብዩ በምዕምናን ከነፍሶቻቸው ይበልጥ ተገቢ ነው፡፡ ሚስቶቹም እናቶቻቸው ናቸው፡፡…… “ ከዚህ ቀጥሎ “እሱም አባታቸው ነው፡፡” የሚለው አረፍተ-ነገር መካተት እንዳለበት ኡቤይ ቢን ካዕብና ሌሎች የጥንት ሙስሊሞች መናገራቸውን አብደላህ የሱፍ አሊ የተባለ የቁርአን ተርጓሚ የቁርአን ትርጉም በሚል መጽሐፉ ጽፎታል፡፡
ሁለተኛው ማስረጃ ደግሞ በአዲሱ የቁርአን ትርጉም(ኡስማን ባሰባሰበው) ሱረቱል አል በቅራህ ቁጥር 238 “በሶላቶች በተለይ በመካከለኛይቱ ሶላት ላይ ተጠባበቁ ታዛዦች ሆናችሁም ለአላህ ቁሙ” ይላል፡፡
ነገር ግን አይሻ እንዳለችው መሀመድ ሲቀራው የነበረው ግን “በሶላቶች በተለይ በመካከለኛይቱ ሶላትና በአል አስር ሶላት ላይ ተጠባበቁ ታዛዦች ሆናችሁም ለአላህ ቁሙ” በሚል ነበር ሲሉ ጃሚ አት ቲርሚዚ ጠቅሰውታል፡፡ ስለዚህ ሶላት አል አስር የምትለዋ ሀረግ በአዲሱ ቁርአን ላይ አልተካተተችም፡፡
ከዚህ በመነሳት ሙስሊሞች በተበረዘና ባልተበረዘ መጽሀፍ መካከል ያለውን ልዩነት አላስተዋሉትም ወይም ማስተዋል አይፈልጉም ማለት ነው፡፡
የተበረዘ መጽሀፍ ዋና ዋና መለያዎች አሉት፡፡
1. የጠፉ ዓረፍተ-ነገሮች አሉት፡፡
2. የጠፉ አንቀጾች ያሉት ነው፡፡
3. የጠፉ ምዕራፎች አሉት
4. የጠፉ አያዎች አሉት፡፡
5. ከጥንት ጽሁፎች ጋር ተቃርኖ ያለው ነው፡፡ ታዲያ ቁርአን እነዚህ ከላይ የተገለጹት መለያዎች ይገልጹታል፡፡ መልሱ በትክክል ይገልጹታል ነው፡፡ ታዲያ አለመበረዝ ማለት ምን ማለት ነው፡፡ ሙስሊሞች መጽሀፋቸው ሳይበረዝ እንደቆየ የሚናገሩት በአፋቸው ብቻ ነው፡፡ ያታሪክ ማስረጃዎቻቸው ግን መበረዙን እያገለጡ ናቸው፡፡ አላህም ቁርአን አንጠብቃዋለን በማለት የማለውን መሀላ መፈጸም አልቻለም፡፡ በቁርአን ሱረቱል ሂጅር ቁጥር 9 “እኛ ቁርአንን እኛው አወረድነው እኛም ለእርሱ ጠባቂዎቹ ነን” የሚለው ቃል ተፈጻሚ አልሆነም ማለት ነው፡፡

No comments:

Post a Comment